Psalms 75

ለመለኮታዊው ዳኛ የቀረበ ዝማሬ

ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዜም፤ የአሳፍ መዝሙር ማሕሌት።

1አምላክ ሆይ፤ ምስጋና እናቀርብልሃለን፤
ስምህ ቅርብ ነውና ምስጋና እናቀርብልሃለን፤
ሰዎችም ስለ ድንቅ ሥራህ ይናገራሉ።

2አንተም እንዲህ አልህ፤ “ለይቼ በወሰንኋት ሰዓት፣
በቅን የምፈርድ እኔ ነኝ።
3ምድርና ሕዝቦቿ ሁሉ በሚናወጡበት ጊዜ፣
ምሰሶዎቿን አጽንቼ የምይዝ እኔ ነኝ። ሴላ
4እብሪተኛውን፣ ‘አትደንፋ’፤
ክፉውንም ‘ቀንድህን ከፍ አታድርግ እለዋለሁ፤
5ቀንድህን ወደ ሰማይ አታንሣ፤
ዐንገትህንም መዝዘህ አትናገር።’ ”

6ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ፣
ወይም ከምድረ በዳ አይመጣምና፤
7ነገር ግን የሚፈርድ እግዚአብሔር ነው፤
እርሱ አንዱን ዝቅ፣ ሌላውን ከፍ ያደርጋል።
8 በእግዚአብሔር እጅ ጽዋ አለ፤
በሚገባ የተቀመመና ዐረፋ የሚወጣው የወይን ጠጅ ሞልቶበታል፤
ይህን ከውስጡ ወደ ውጭ ገለበጠው፤
የምድር ዐመፀኞችም አተላውን ሳይቀር ይጨልጡታል።

9እኔ ግን ይህን ለዘላለም ዐውጃለሁ፤
ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬ አቀርባለሁ።
10የክፉዎችን ሁሉ ቀንድ እሰብራለሁ፤
የጻድቃን ቀንድ ግን ከፍ ከፍ ይላል።
Copyright information for AmhNASV